ፍሬንድስ ፎር ቺልድረን (ኤፍኤፍሲ) ፖለቲካዊም ሃይማኖታዊም ያልኾነ የኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው። የድርጅቱ ዐበይት ዐላማዎች የሚከተሉት ናቸው፤
- በ-ኤቻይቪ/ኤድስ ሳቢያ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው የኢትዮጵያውያን ልጆችን የድኽነት፣ የመከራ እና የአእምሮ ሥቃይ ለማቃለል የገንዝብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ መስጠት፤ ደግሞም ኹኔታዎች ሲፈቅዱ
- ለዕጓለ-ማውታ እና ለጐዳና ተዳዳሪ ልጆች ድኅንነት እና መብት የሚለፉ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶችን በምክር እና በገንዘብ/ቁሳቁስ ርዳታ ማገዝ።
እኒህን ዐላማዎቹን በተግባር ለመፈጸም ፍሬንድስ ለዕጓለ-ማውታዎች አንድ የገንዘብ ድጋፍ (sponsorship) ፕሮግራም እያካኼደ ይገኛል። የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሙ ምንም የዘውግ፣ የሃይማኖት፣ የጾታ ወይም የፖለቲካ ልዩነት ሳያደርግ ለዕጓለ-ማውታዎች ርዳታ ያቀርባል። በርግጥ ድርጅቱ ባሉበት የገንዘብ እና ሌሎች ውሱንነቶች የተነሣ አኹን የሚያካኺደው ፕሮግራም በዐዲስ አበባ የተገደበ ነው፤ እጅግ በጣም ትልቁ የዕጓለ-ማውታ ክምችት በሚገኝበት የሀገሪቱ መዲና። ወደፊት ግን ከገንዘብ ዐቅሙ መጐልበት እና ከድርጅታዊ ክሂሎቱ (organisational capacity) ማደግ ጋር የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሙን በኹሉም የሀገሪቱ ክልሎች የመዘርጋት ዕቅድ አለው።
ስለ ፍሬንድስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እባክዎ ይህን ማገናኛ በመጫን በተደጋጋሚ ለሚነሡ ጥያቄዎች ያዘጋጀነውን ሰነድ ይመልከቱ።