ስለ እኛ
ፍሬንድስ ፎር ችልድረን (ኤፍኤፍሲ) ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው። ኦክስፈርድ በምትባል የእንግሊዝ ሀገር ከተማ ውስጥ ኗሪ የኾኑ ጥቂት ጓደኛሞች በመስከረም 1997 ዓ.ም (ሴፕቴምበር 2003) የፈጠሩት አንድ ቡድን ነበር። ይህን ቡድን መሠረት በማድረግ ግብረ-ሠናይ ድርጅቱ ተቋቋመ። የድርጅቱ ዐላማ የ-ኤቻይቪ/ኤድስ ወረረሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ባደረሰው ታላቅ ጥፋት የተነሣ ወላጅ-አልባ በኾኑ አእላፍ ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ እና ግፍ ለማቈም የሚያግዝ አንድ የባሕር ማዶ ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር ነው። በበሽታው የተነሣ ወላጆቻቸውን ያጡ ዕጓለ-ማውታ ቍጥር በፍጥነት ማደግ እጅግ አሳሳቢ ጕዳይ ነው። በዋና ከተማዋ ዐዲስ አበባ ብቻ በበሽታው ወላጆቻችውን ያጡ ዕጓለ-ማውታ ብዛት በዐሥር ሺዎች ይቈጠራሉ። እኒህ በድኽነት የተጐሳቈሉ፣ በአካል እና በመንፍስ የተጐዱ ልጆች ለእንግልት፣ ለብዝበዛ እና ለመድልዎ የተጋለጡ ናቸው። ለወትሮው ልጆችን በመጠለል እና ከክፉ ነገር በመጠብቅ ረገድ ከቤተሰብ በተጨማሪ ጐረቤቶች እና ዘምድ-አዝማድ የጐላ ድርሻ ነበራቸው። ይህ ባህላዊ የማኅበረሰብ ድጋፍ ሥርዐት ባለንበት ዘመን ድርሻውን ለመፈጸም ተስኖታል፤ የልጆቹ ቍጥር ከልክ ማለፍ ባስከተለው ጫና የተነሣ። በአስከፊ ድኽነት እየተመናመነ የነበረው የማኅበረሰቡ የሰው እና የገንዘብ ዐቅም እጅግ ለበዙት ወላጅ አልባ ልጆች የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ርዳታ ለማቅረብ እንዳይችል አድርጎታል።
ፍሬንድስ አኹን በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ (በቁጥር 1115193የተመዘገበ)፣ በቍጥር አነስተኛ በዐላማ ግን ቍርጠኛ የኾኑ አባላት እና ደጋፊዎች ያሉት ድርጅት ነው። አባላቱ በጎ ዐላማውን ከሚደግፉ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገሮች ዜጎች የተወጣጣ፤ ተማሪዎችን እና ባለሙያዎችን፣ ወንዶች እና ሴቶችን፣ ወጣቶች እና አዛውንትን የሚያካትት ነው። የድርጅቱም ደጋፊዎች ወተር (network) እንዲሁ ልይዩ እና ኹሉን አሰባሳቢ ነው። ደጋፊዎቹ ለድርጅቱ ህልውና ዐቢይ ሚና ይጫወታሉ፤ የገንዝብ ርዳታ ከማድረጋቸውም በላይ ከዕክብ ግንባታ (fundraising) እስከ ማስተዋወቅ ሥራ ባሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋሉ።
ግብረ-ሠናይ ድርጅቱ በ-ኤቻይቪ/ኤድስ የተነሣ ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆች የገንዘብ ድጋፍ መስጫ አንድ ፕሮግራም ጀምሯል። ፕሮግራሙ የተቀረጸው እንደ ምግብ፣ ልብስ እና የትምህርት ቍሳቍስ መግዣ ዐይነት የመፍቅድ ወጪዎችን የሚሸፍን የገንዘብ ርዳታ በመስጠት ተረጂዎቹ ልጆች በዘመዶቻቸው ቤተሰብ ውስጥ በፍቅር እና ክብካቤ እንዲያድጉ ለማስቻል ነው። ፕሮግራሙ ታኅሣሥ 1997 (December 2004) ሦስት ልጆችን በመደገፍ የጀመረ ሲኾን፣ ከጥር 2003 ጀምሮ (since January 2010) በአማካይ 40 ልጆችን በመደገፍ የማይናቅ እድገት አሳይቷል።
ይህንን ዐላማውን ከግቡ ለማድረስ ፍሬንድስ ለልጆች ክብካቤ እና ደኅንነት ከሚጥሩ ግበረ-ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሠራል። በአኹኑ ጊዜ ፍሬንድስ «ሪዲም ዘ ጀነሬሽን» እና «ኢሳፕሶ» (ISAPSO) ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል። ኹለቱም ዐዲስ አበባ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ድርጅቶች ሲኾኑ፤ ለዕጓለ-ማውታ ሕፃናት እና ለጐዳና ተዳዳሪ ልጆች የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ያካኺዳሉ፤ ለምሳሌ ያኽል የሕፃናት ማሳደጊያዎችን ወይም የወጣቶች መኖሪያዎችን ያስተዳድራሉ፤ የምግብ፣ የጤና እና የትምህርት ድጋፍ ይሰጣሉ፤ በቅርብ ዘመዶች ክብካቤ ለሚያድጉ ልጆች የሚሰጥ የገንዝብ ድጋፍ ፕሮግራምን ያስፈጽማሉ።
ፍሬንድስ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ያልኾነ ድርጅት ነው፣ ዐላማዎቹ እና ግብ መምቻዎቹም የሚያነጣጥሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዕጓለ-ማውታ እና የሌሎች ለአደጋ የተጋለጡ ልጆችን ችግሮች በማቃለል ላይ ነው። ፍሬንድስ ሙሉ በሙሉ በፍቃደኞች የሚንቀሳቀስ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ነው፤ እንዲያ በመኾኑም ምንም የድርጅት ማንቀሳቀሻ ወጪ የለበትም። ከመደበኛ መዋጮ፣ ከደጋፊዎች የገንዘብ ስጦታ፣ ከዕክብ ግንባታ (fundraising) የሚሰበሰበው እጅግ አብዛኛው ገንዘብ ለዕጓለ-ማውታ መርጃ የሚውል ሲኾን፣ ቀሪው ደግሞ ትንንሽ አስፈላጊ ወጪዎችን ይሸፍናል፤ (የባንክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያዎች፣ እንዲሁም የማስተዋወቂያ፣ የኅትመት እና የጽሕፈት መሣሪያ ወጪዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ)።