ፕሮጄክቶቻችን

የገንዘብ ድጋፍ መስጫ ፕሮግራም

ዋናው ፕሮጀክታችን ኢትዮጵያ ውስጥ በ-ኤቻይቪ/ኤድስ የተነሣ ወላጆቻቸውን ላጡ ዕጓለ-ማውታዎች የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ነው። ለጊዜው ይህ ፕሮጄክት ዐዲስ አበባ ላይ ያተኵራል፤ የድርጅቱ የገንዘብ እና የሰው ጥሪት በሚፈቅደው ጊዜ ግን የመላ ሀገሪቱ ክልሎችን የሚሸፍን ይኾናል።

የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሙ ትኵረት ኹለቱንም ወላጆቻቸውን ባጡ፣ ግን በቅርብ ዘመዶች (እንደ አያት፣ ታላቅ ወንድም ወይም እኅት፣ አክሥት፣ አጎት፣ ወዘተ. ባሉ ዘመዶች) ክብካቤ ማደግ በሚችሉ ልጆች ላይ ነው። ፍሬንድስ በእንደዚህ ያለ ኹኔታ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ተረጂዎቹ ልጆች ፍቅር በተሞላበት የቤተሰብ ከባቢ ማደጋቸውን ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርገው ያምናል። እንዲህ ዐይነቱ ድጋፍ ባህላዊውን የቤተዘመድ እና የማኅበረሰብ ድጋፍ ሥርዐት ያግዛል፤ ዕጓለ-ማውታዎችን እና ለአደጋ የተጋለጡ ልጆችን ዐቅፎ-ደግፎ መያዣው ባህላዊው ዘዴ እርሱ ነበርና። አሳዳጊ መኾን የሚችሉ ዘመዶችም ለራሳቸውም ኾነ ለሌሎች ጥገኞች ማኖሪያ በቂ የንዋይ ዐቅም ስለማይኖራቸው የገንዘብ ድጋፉ ለእነርሱም ያጋጣሚ ጥቅም አቅራቢ ይኾናል።

የፕሮግራሙ አፈጻጸም እንዲህ ነው። በቂ የገንዘብ ዕክብ ባለን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊነት እየተንቀሳቀሱ ዕጓለ-ማውታ እና ሌሎች ለአደጋ የተጋለጡ ልጆችን ከሚረዱ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እናደርጋለን። ባወጣነው መስፈርት መሠረት ለስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም ብቁ የኾኑ ልጆችን መርጠው እንዲልኩልን እንጠይቃለን። የልጆቹን ብቁነት ስናረጋግጥ እና በውል ደንቦች እና አግባቦች ስንስማማ፣ ከሸሪክ ድርጅቶቹ ጋር የመግባቢያ ሰንድ እንፈርማለን፤ የተቀበልናቸውም ልጆች ወርኃዊ አበል ማግኘት ይጀምራሉ። ፍሬንድስ በየስድስት ወሩ ፕሮግራሙን ለሚያስተዳድሩ ሸሪክ ድርጅቶቹ ገንዘብ ያስተላልፋል። ድርጅቶቹ አበሉን በየወሩ ልጆቹን በክብካቤ ለሚያሳድጉ ዘመዶች ይከፍላሉ፤ የልጆቹን ደኅንነት ይከታተላሉ፤ ስለ እያንዳንዱ ተረጂ ልጅም የመንፈቅ እና የዓመት ዘገባ ለፍሬንድስ ያቀርባሉ። በተጨማሪ የኛ ተወካይ ወይም አባሎች ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙ ጊዜ ልጆቹን እና አሳዳጊዎቻቸውን ለመጐብኘት ቢፈልጉ ሸሪክ ድርጅቶቹ ርዳታ ያደርጋሉ። ስፖንሰር የምናደርጋቸውን ልጆች መጐብኘት የሚቻለው ቢያንስ የልጆቹ አሳዳጊዎች፣ አሊያም የኛ ተወካይ ወይም የሸሪክ ድርጅቱ ባልደረባ በሚገኝበት ቦታ እና ጊዜ ብቻ ነው።

ለሸሪክ ድርጅቶች (Partners) ድጋፍ መስጠት

የፍሬንድስ አባላት ባመቸ ጊዜ እና ቦታ ኢትዮጵያ ለሚገኙት ሸሪክ ድርጅቶች ምክር በመስጠት እና የሙያ-ነክ ልምድ በማካፈል ርዳታ ያደርጋሉ። እነዚህ ድርጅቶች፣ ብዙውን ጊዜ፣ የየዕለት ተግባሮቻቸውን ለመከወን ከፍተኛ የገንዝብ ዕጥረት አለባቸው፤ በጣም አስፈላጊ የኾኑ ቁሳቁስ እና ሙያተኞችም አይኖሯቸውም። በሌላ በኩል ፍሬንድስ የማይናቁ የሙያ ልምዶች ያካበቱ አባሎች እና ደጋፊዎች አሉት። ብዙ አባላቱ ጠቃሚ የመረጃ እና የቁሳቁስ ምንጮችን በቀላሉ ማግኘት በሚችሉባቸው ከባቢዎች ውስጥ ይገኛሉ። በሸሪክ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ተዛማጅ ዕጦቶችን እስከተቻለ ለማሟላት ምክር/ልምድ ለማቅረብ ወይም ለማጋራት ፍቃደኞች ናቸው።
ከዚህ ቀደም የፍሬንድስ አባላት ከሸሪክ ድርጅቶች ለአንዱ የምክር እና የቴክኒክ ድጋፍ ሰጥተው ነበር። በአኹኑ ጊዜ ደግሞ ድርጅቱ ለሸሪክ ድርጅቶች ፕሮጄክቶች የለጋሾችን ድጋፍ ለማስገኘት በመሞከር ላይ ነው።

በተጨማሪ ከነዚህ ሸሪክ ድርጅቶች ውስጥ የኢንተርኔት ህልውና የሌላቸው ወደፊት ይኖራቸው ዘንድ ፍሬንድስ የዚህ ድርቀዬው (ዌብሳይት) ንኡስ አካል የኾኑ ሱብዶሜይን ሊፈጥርላቸው ያስባል። ስብዶሜይን ድርጅቶቹ ራሳቸውን እና አስደናቂ ሥራዎቻቸውን ለፍሬንድስ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም ከባሕር-ማዶ ኗሪ ለኾኑ ኢትዮጵያውያን ኹሉ የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ያምናል።