በፍሬንድስ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል

ፍሬንድስ ፎር ቺልድረን በጣም ትንሽ ድርጅት ነው። ብዙውን አሰተዳደራዊ ሥራ በሚከውኑ ሦስት ሥራ-ስኪያጅ አባላት ይንቀሳቀሳል። እኒህ ኀላፊዎች ግዴታቸውን በትርፍ ጊዜዎቻቸው ይከውናሉ። ድርጅቱ የአስተዳደር ሥራውን የሚከውኑ ሠራተኞች ለመቅጠር ገንዘብም ኾነ ፍቃደኛነት የለውም። ይህም የሥራ ማስኬጃ ወጪን በተቻለ መጠን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚከተለውን መርሕ ለመጠበቅ ነው። እንዲህ በመኾኑ የግብረ-ሠናይ ድርጅቱ መጻኢ በአባላቱ የማያቋርጥ የገንዘብ ድጋፍ እና በበጎ ፈቃደኞች ርዳታ – ገንዘብ በማሰባሰብ እና ተርጋራዊ ድጋፍ በመሰጠት የሚደረግ ርዳታ – ላይ ይመረኰዛል።

ለዕክብ ግንባታ በፍቃደኛነት ይካፈሉ

እስካኹን የተደረጉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ እንቅሳቃሴዎች ጥቂት ናቸው። በድርጅቱ አባላት እና በደጋፊዎች የተደረጉ ነበሩ። በዚህ ረገድ አመርቂ እንቅስቃሴ አልተደረገም። ስለዚህ ድርጅቱ በዕክብ-ግንባታ ሥራ ላይ የሚያተኵር በጎ-ፍቃደኛ ወይም አንድ የበጎ-ፍቃደኞች ቡድን ያስፈልገዋል። የፍቃደኞች ተሳትፎ የድርጅቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ድርጅቱ ለዕጓለ-ማውታ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲስፋፋ ለማድረግ ትልቅ ተዋጽኦ ይኖረዋል።

ተግባራዊ ድጋፍ ይስጡ

ተግባራዊ ድጋፍ በፍሬንድስ ሥራ-አስኪያጆች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ የሚችልበት በርካታ ዘርፎች አሉ። ከነዚህ ጥቂቱ የባለሙያ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። በተለይም

  • የፕሮጄክት እቅድ መጻፍ
  • ዓመታዊ ጉባኤ ማዘጋጅት
  • የፍሬንድስን ድር-ቀዬ ….
  • የማስተዋወቂያ ቍሳቍስ ማዘጋጀት

ለድርጅታችን ከፍተኛ ርባና አላቸው። በነዚህ እና በመሰል ተፈላጊዎች ረገድ ያለብን ዕጥረት – የሙያ ችሎታ እና የቍሳቍስ ምንጭ ዕጦት – እንቅስቃሴዎቻችን እና የማደግ ዕድላችንን እየገቱብን ናቸው። በነዚህ ተግባሮች ዙሪያ የሚደረግ የፍቃደኞች ተሳትፎ ፍሬንድስን ይጠቅማሉ። ሊረዱን የሚችሉ ከኾነ፣ እባክዎ ያግኙን።

በገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ይሳተፉ

የፍሬንድስ ዋናው ፕሮጄክት ኹለቱንም ወላጆቻቸው በ-ኤቻይቪ/ኤድስ የሞቱባቸውን ሕጻናት በገንዘብ መደገፍ ነው። በአኹኑ ጊዜ በኛ የሚደገፍ ልጅ ወርኃዊ አበል ያገኛል። አበሉ እንደ ምግብ፣ ልብስ እና የትምህርት ቁሳቁስ ያሉ መሠረታዊ መፍቅዶችን ለማግኘት የሚያስፈልገውን ወጪ በመጠኑ ይሸፍናል፤ እንዲያም ሲል ልጁ በሚንከባከበው ዘመድ ቤት እየኖረ ትምህርት እንዲከታተል ያስችለዋል።

በፕሮግራማችን የተያዘ አንድ ልጅ መሠረታዊ ድጋፍ ያገኝ ዘንድ በአማካይ ዩኬፓ 15.00 (ዐሥራ-ዐምስት ፓውንድ ስተርሊንግ) ይበቃል። በተለምዶ መደበኛ የገንዘብ ተዋጽኦ ለማድረግ የሚፈልግ ሰው አባላችን ይኾናል። የአባሉ መዋጮ ደግሞ ወደ አጠቃላይ የድርጅቱ የገንዘብ ዕክብ ይገባና ለልጆች መደገፊያ ይኾናል። የምንደግፋቸው ልጆች ብዛት በዕክባችን መጠን ይወሰናል።

የፍሬንስድ አባል ለመኾን የተወሰነ የገንዘብ መጠን የለም። የአባሎቻችን ማኅበረሳባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዳራ በጣም ሰፊ ነው። በዕድሜም በኹሉም እርከን የሚገኙ ናቸው፤ ከተማሪ  ልጆች እስከ ጡረተኞች የሚካተቱበት። እንዲያ ስለኾነም ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን መዋጮ ያደርጋሉ። ፍሬንድስ ስለ እያንዳንዷ የሳንቲም ወይም የፓውንድ መዋጮ አመስጋኝ ነው፤ ሳንቲሞች ተደማምረው ርዳታ የሚያስፈልገውን ልጅ በገንዘብ ለመደገፍ ይበቃሉና።